View Full Version : የአፍሪቃ-ቅርምት ጉባኤ 125ኛ አመት- እፍረተ በዓል


lamrof
February 17th, 2010, 06:00 AM
የአፍሪቃ-ቅርምት ጉባኤ 125ኛ አመት
ቢስማርክ-የጉባኤዉ መሐንዲስ
«ብዙ ጊዜ በታሪክ ለሚፈፀሙ በደሎች የገንዘብ ካሳ ይከፈላል። ለዚሕስ (ግፍ) ካሳ የማይከፈልበት ምን ምክንያት አለ?

23 11 09

የጀርመኖች የዳግም ዉሕደታቸዉ ቅድመ ብሥራትና፣ የድፍን አለም ኮሚንዝም ዉድቀት ሃያኛ አመት ከብረ በዓል በርሊን ላይ በተከበረ በሳምንቱ፣

እንዲሁም የተባበሩት መነግስታት ድርጅት ችግር ለጠናበት አፍሪቃዊ የለጋሹን እርጥባን የጠየቀበት ጉባኤ ሮም ላይ በተሰየመበት ዕለት፣

በተጨማሪም ከበርሊን በሚነሳ እሳት በተደጋጋሚ የተለላለቁት አዉሮጳውያኖች፣ የፍጅት ምክንያት የነበረዉን ልዩነታቸዉን አስወግደው፣ የህብረታቸውን ፅናት ምልከት፣ አንድ የጋራ መሪ ለመምረጥ ባቀዱበት የ4 ቀን ዋዜማ

እነሆ ዘሬ በበርሊን ከተማ አፍሪቃን ያቀራመተዉ የጅቦች ጉባኤ አንድ መቶ ሃያ-አምስተኛ አመት እፍረተ-በዓል በመላው አለም ይ'ተ'ወሳል።


አፄ-ምኒሊክ የመሩት ኢትዮጵያዊ ህዝብ ነፃነቱን ለማስከበር የከፈለዉ መስዋዕትነትና በኢጣሊያ ቅኝ ገዢዎች ላይ የተቀዳጀዉ ድል ለኢትዮጵያዊዉ አኩሪነቱን፣ ለድፍን ጥቁር ሕዝብ የነፃነት አለኝታነቱን፣ የጊዜ ህልፈት የሚሽረው አይደለም።

ከክዋሚ ንኩሩማ እስከ ጆሞ ኬንያታ፣ ከሴዳር ሴንጎር እስከ ጁሊየስ ኔሬሬ፣ ከሮበርት ሙጋቤ እስከ ኔልሰን ማንዴላ የመሩት አፍሪቃዊ፣ በቅኝ ገዢ ዘረኛ ገዢዎቹ ላይ ላመፀበት ዘመን፣ ለታገለበት ሥልት፣ ለከፈለዉ መስዋእትነት፣ ለትግሉና ለድሉ ቆስቋሽ አብነት የሆነው-የአድዋ ድል- አነሳሱ ፀረ ቅኝ አገዛዝ፣ አላማው ነፃነት መሆኑ አያነጋግርም።

ቀዳማዊ ንጉስ ኡምቤርቶን ለቅኝ ገዢነት ያጃገነዉ፣ ንጉስ ቪክቶር ኢማኑኤል ሳልሳዊን ከነጀኔራሎቻቸዉ አድዋ ላይ የቅኝ ግዢነት እብሪት እንዲያናወዛቸዉ የዳረጋቸው ጉድይ፣ በ1884 (ዘመኑ በመሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) በርሊን ላይ የተደረገው የቅርምት ጉባኤ ነበር።

ከሕዳር አስራ-አምስት 1884 እስከ እስከ የካቲት አጋማሽ 1985 የዘለቀዉ ጉባኤ ከተሰየመበት አዳራሽ አጠገብ-አንዲት የመታሰቢያ ሰሌዳ ቆማለች። ሰሌዳዉን ያቆመዉ የቶጎዉ ተወላጅ-ቪክቶር ድሲድሶኑ የያኔዉን ታሪክ አፍሪቃዉያን መዘንጋት የለባቸዉም-ባይ ነዉ።

«ሠሌዳዉ ለኔ በጣም አስፈላጊ ነው ምክንያቱም የአፍሪቃን ታሪክ በሙሉ ሥለተከታተልኩት፣ ዛሬ አፍሪካ ውስጥ ያለዉን ችግር ያኔ ከተፈፀመዉ ጉዳይ ጋር ማገናኘት ሥለምሻ ነዉ። ይሕ ሰሌዳ በቅኝ አገዛዝ ዘመን የተፈፀመዉ በደል እንዳይረሳ ማስታወሻ እንዲሆን እፈልጋለሁ። ለዚሕም ነዉ ያኔ አፍሪቃን በተቀራመቱባት ሥፍራ መቆም አለበት ብዬ ያሰብኩት።»

የፖርቱጋል፣ የቱርክና የስፓኝ ቅኝ ገዢዎች ክንድ እየዛለ፣ የብሪታንያና የፈረንሳይ እየፈረጠመ በነበረበት በአስራ ዘጠነኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ነባሮቹ ብዙ እንዳይበለጡ ዘግየት ብለዉ ከጎለበቱት እንደ ጀርመንና ኢጣሊያ ከመሳሰሉት ጋር ማበሩን እንደ ጥሩ ብልሐት አይተውት ነበር።

ኢጣሊያ ከኦስትሪያ-ሐንጋሪ እና ከጀርመን ጋር የጦር ቃል ኪዳን ስትፈራረም፣ የቤልጂጉ ንጉስ ሊዮፖልድ ሉዊስ ፊሊፕ ቪክቶር ዳግማዊ የዛሬዋን ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክን በ1878 እንደ ግል-ርሰተ ጉልታቸዉ መግዛት መጀመራቸዉ ብዙዎቹን ቅር አሰኝቶ ነበር። በተለይ ፈረንሳይ የሊዮፖልድን እርምጃ መደገፏ የፖርቱጋልና የብሪታንያን ቁጣ ቀስቅሶ ነበር።

ፖርቱጋሎች ጉዳዩን ለማገድ ከጀርመኖች ጋር መተባበሩን ሲመርጡ፣ ጀርመናዊዉ የታሪክ አዋቂ ዮአኺም ሴለር እንደሚሉት «ብረቱ» የሚል ቅፅል ለታከለላቸዉ ለጀርመኑ መራሔ መንግሥት ለኦቶ ፎን ቢስማርክ ሾንሐዉሰርና ለወዳጆቻዉ ጥሩ አጋጣሚ ነበር።

«ኮንጎ በሊዮፖልድ ዳግማዊ እጅ መዉደቋና በዚያ በኩል የሚደረገዉ የሸቀጥ ዝዉዉር መታገዱ ለቢስማርክና ለሌሎቹ አሳሳቢ ነበር። የብዙዎቹ እምነት መርከቦች በኮንጎ ወንዝ በመነፃ መዘዋወር ይቻላቸዋል፣ ሌሎች ሐያል መንግሥታትም ወደ ኮንጎ የመግባት መብታቸዉ መጠበቅ አለበት የሚል ነበር።»

የኮንጎ ድልብ ሐብት ሰበብ፣ የቅኝ ገዢዎቹ ልዩነት፣ የአዳዲሶቹ ሐይላት ጥያቄ፣ እንዲሁም የእርስበራሳቸዉ መፈራራት ጉዳይ አፍሪቃን የመቀራመቱ ፍላጎት መሠረት ሆነ። ቢስማርክ ያን ጉባኤ ጠሩ። ሶስት ወር በቆየዉ ጉባኤ አስራ ሁለት የአዉሮጳ ሐገራት፣ ቱርክና ዩናይትድ ስቴትስ ተካፋዮች ነበሩ።

ሐያላኑ ሃገራት የአፍሪቃን ካርታ ጠረጴዛ ላይ ዘርግተው አፍሪቃን ሲቀራመቱ፣ ሴለር እንደሚሉት አንድም አፍሪቃዊ አልተወከለም ነበር።
«በግልፅ መታወቅ ያለበት አንድም አፍሪቃዊ (በዚያ ጉባኤ) እንዲገኝ አልተጋበዘም ነበር።»

ያኔ አይደለም ዛሬም የዚያን ዘመኑን ታሪክ የሚያስብ አፍሪቃዊ መሪ የለም፣ ካ'ለ'ም አይታወቅም። እንደ ጀርመንና ኢጣሊያ ያሉት ባነሱት ጥያቄ ብዙም ካልተደሰቱት አንዷ ብሪታንያ ከአፄ ዩሐንስ ጋር የሔዉሌት ስምምነት የተባለዉን ዉል አድዋ ላይ ተፈራርማ ነበር። ዉሉ ኢትዮጵያ ምፅዋንና የመሳሰሉትን ወደቦች እንድትጠቅም ብሪታንያ እዉቅና የሰጠችበት ነዉ።

በርሊን ላይ ከነኢጣሊያና ጋር እተደራደረች፣ አድዋ ላይ ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር የተዋዋለችዉ ብሪታንያ፣ የበርሊኑ ጉባኤ ባበቃ በወራት እድሜ ኢጣሊያ ምፅዋን ስትቆጣጠር፣ ለደካማዋ ኢትዮጵያ ለፈረመችዉ ዉል ፅናት አልተከራከረችም። በርግጥም ጥቅም የሐይልን ሚዛን አሰላለፍ በሚወስንበት፣ እልፍ ሲልም የዘር-ወገን ቅርበት በሚቆጠቁጥበት የፖለቲካ ጨዋታ፣ ሐቅ፣ ቃልና፣ ሥነ ምግባር ቦታ አልነበራቸውም።

የበርሊኑ ጉባኤ ልዩነት ድብልቅልቁ ወጥቶ አንደኛና ሁለተኛ በሚባሉት ጦርነቶች አለም እስከነደደችበት ግዜ ድረስ የድፍን-አፍሪቃ ሕዝብ በቅኝ ገዢዎች ሐያላት ተጨፍጭፏል፣ ተረግጧል፣ ተገድሏል፣ ተዋርዷል። እስከዛሬ ለተረፈ የርስ በርስ ግጭትም ተዳርጓል።

ከሕዳር አስራ-አምስት ጀምሮ በርሊን ዉስጥ በሚካሔደዉ ስብሰባ ላይ ከሚካፈሉት አፍሪቃዉያን አንዱ ስቬን ሜካሪደስ እንደሚለዉ በቅኝ አገዛዝ ዘመን በአፍሪቃዉያን ላይ ለተፈፀመዉ በደል-ካሳ የማይከፈልበት ምክንያት አይገባዉም።

«ብዙ ጊዜ በታሪክ ለሚፈፀሙ በደሎች የገንዘብ ካሳ ይከፈላል። ለዚሕስ (ግፍ) ካሳ የማይከፈልበት ምን ምክንያት አለ? ባሁኑ ጊዜ በየሥፍራዉ የገንዘብ እጥረት መኖሩ ይገባኛል። ይሁንና እዉነተኛ የምጣኔ ሐብት ትብብር ማድረግ የሚገድ አይመስለኝም። የያኔዎቹ ቅኝ ገዢዎች አፍሪቃዉያንን ለማስተማርና ለማሰልጠን ወጪ የሚሆን የገንዘብ ተቋም መመሥረት ይላሉ።»

ይችላሉ ግን-ለምን ያደርጉታል። ማንስ ጠይቋቸዉ።

አዉሮጶች የጦርነትን ምክንያትን አስወግደዉ ዛሬ አንድም ብዙም ሆነዉ አለምን መምራታቸዉ ብዙ አይገርምም። እስከ 1990ዎቹ ድረስ ሥለ-ድሕነት፣ በሽታ እና ረሐብ ሲነሳ አፍሪቃ፣ እስያ፣ ደቡብ አሜሪካ እንደቅደም እኩል ተጠቃሾች ነበሩ። ዛሬ ግን ደቡብ-አሜሪካ እና እስያዎች በረሐብ፣ በበሽታና በጦርነት የሚያልቅ ሕዝባቸዉን ቁጥር ቀንሰዉ ፖለቲካዊ መብት እኩልነታቸዉን እያስከበሩ ነዉ። የሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ዉዝግብ በድርድ ይፈታ ቢባል፣ ከስድስቱ ተደራዳሪዎቹ አራቱ እስያዎች ናቸዉ። የሁንዱራስ ፖለቲከኞች ቢወዛገቡ፣ ግንባር ቀደም ሸምጋዮች እነ ብራዚል ናቸዉ። አፍሪቃ ግን በነበረችበት ናት።

በየአመቱ በሃያ-በሰላሳ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ የሚራብባት አፍሪቃ-የምግብ ምፅዋት ከመለመን አልፎ ላለፈ በደል ካሳ የሚሟገት፣ ለዛሬ መብት እኩልነት፣ ለወደፊት ብልፅግና የሚታትር መሪ አላት ማለት በርግጥ ያዳግታል። የዚምባቡዌ የኬንያ፣ የጊኒ፣ ሌላዉ ቀርቶ ነፃነትዋን አስከብራ በመኖርዋ የምትኮራዉ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ደም-አፋሳሽ ዉዝግብ ንትርካቸዉን መፍታት አቅቷቸዉ የለንደንን፣ የዋሽንግተንን፣ የብራስልስን እና የመሳሰሉትን ዉሳኔ እየጠበቁ አፍሪቃ በባሪያ ፈንጋይ ቅኝ ገዢዎች ተበድላለች የሚሉበት ልቡና ከየት ያመጣሉ?

ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

lamrof
February 17th, 2010, 06:23 AM
http://farm5.static.flickr.com/4038/4363888939_f32a591b64_o.jpg