View Full Version : የመድረክ አመራሮች የመንግሥትን የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አጣጣሉት


lamrof
September 17th, 2010, 02:03 AM
‹‹ዕቅዱ የሕዝቡን አመለካከት መለወጫ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ነው›› ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው
‹‹በበሬ እየታረሰ ከፍተኛ እመርታ ማስመዝገብ አይቻልም›› አቶ ገብሩ አስራት
‹‹ኢሕአዴግ በያዛቸው ካድሬዎች ዕድገት ያመጣል ብሎ ማሰብ በህልም ደረጃም ያስቸግራል›› ዶክተር መረራ ጉዲና (በኃይሌ ሙሉ)

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ አመራሮች መንግሥት በቅርቡ ያስተዋወቀውን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ባለፈ ተፈጻሚ ይሆናል የሚል ዕምነት እንደሌላቸው ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

የመድረክ ሊቀመንበር ኢንጅነር ግዛቸው ሽፈራው እንደገለጹት፣ ከኢሕአዴግ መንግሥት የልማት አፈጻጸም ታሪክ አንጻር ሲታይ መንግሥት ያዘጋጀው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ያለፈ ውጤት አይኖረውም፡፡

‹‹ልማትና ዕድገት የሚመጣው ከዴሞክራሲ፣ ከፍትሕ ሥርዓትና ከሰብዓዊ መብት መስፈን ጋር ተያይዞ ነው፤›› ያሉት ኢንጅነር ግዛቸው፣ ደርግ አረንጓዴው ዘመቻ በሚል የልማት ዕቅድ ነድፎ የነበረ ቢሆንም፣ ረሃብን ከማባባስ ውጪ ውጤት አለማግኘቱን፣ በተመሳሳይም የኢሕአዴግ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ‹‹ሕዝቡን በምግብ ራሱን እንዲችል አደርጋለሁ›› ብሎ ሕዝቡን በተስፋ ቢሞላም ሳይሳካለት መቅረቱን ተናግረዋል፡፡

እንደ ኢንጅነር ግዛቸው ገለጻ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ባልሰፈነበት ሁኔታ የታቀዱ ዕቅዶች ተግባራዊ የመሆናቸው ዕድል የጠበበ ነው፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ከአምስት ዓመት በፊት በነደፈው መርሐ ግብር የአገሪቱ ሕዝብ በምግብ ራሱን እንደሚችል ገልጾ እንደነበር ያስታወሱት ኢንጅነር ግዛቸው፣ በ2002 ዓ.ም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት የተረጂዎች ቁጥር በ1997 ዓ.ም. ከነበሩት ተረጂዎች በ500 ሺሕ ብቻ ቀንሶ ሰባት ሚሊዮን መድረሱን ተናግረዋል፡፡

ኢሕአዴግ የአምስት ዓመቱን መርሐ ግብር በ1997 ዓ.ም ሲያዘጋጅ የአገሪቱ አጠቃላይ የሰብል ምርት 130 ሚሊዮን ኩንታል የነበረ መሆኑንና በመርሐ ግብሩም መንግሥት የአገሪቱን የሰብል ምርት 320 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ አቅዶ እንደነበር የጠቆሙት ኢንጅነር ግዛቸው፣ የአምስት ዓመቱ መርሐ ግብር ሲጠናቀቅ ከታቀደው የ190 ሚሊዮን ጭማሪ 50 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ መሳካቱን አስረድተዋል፡፡

እንደ ኢንጅነር ግዛቸው ገለጻ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዋነኛ ችግር የዴሞክራሲ ጉድለት ነው፡፡ ሰው በነፃ አስቦ በነፃ እስካልተንቀሳቀሰ ድረስ ዕቅዱ ይፈጸማል ብሎ ማሰብም ከእውነት የራቀ ተስፋ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ዕድገት ከፍትሕ ሥርዓትና ከነፃ አስተሳሰብ ጋር የተገናኘ መሆኑን ሲያመለክቱም፣ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ያልሆኑ አገሮች ሁልጊዜ እንደተራቡ ነው፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የገነቡ አገሮች ግን ሲራቡ አይታዩም፤›› ብለዋል፡፡

አይይዘውም፣ ‹‹እንደ ዜጋ አገሪቱን ከረሃብና ከልመና አውጥቶ ሕዝቡ የተሻለ ቤትና የተሻለ ልብስ እንዲያገኝ እንፈልጋለን፤ ነገር ግን የሕዝቡ ሕይወት አልተለወጠም፡፡ ረሃብተኞች በዝተዋል፡፡ ዕቅዱ የሕዝቡን አመለካከት መለወጫ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ነው፤›› በማለት ዕቅዱ ተፈጻሚ ይሆናል የሚል ዕምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ ሊቀመንበርና የመድረክ አመራር አባል ዶክተር መረራ ጉዲናም በኢንጅነር ግዛቸው ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ ‹‹ዕቅዱ ኢሕአዴግ የከፈተው አዲስ የፕሮፓጋንዳ አቅጣጫ ይመስላል፤›› ያሉት ዶክተር መረራ፣ በአሁኑ ጊዜ ኢሕአዴግ ያቀደውን የ15 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ሊያመጣ የሚያስችል የሰው ኃይል የሌለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሙስና በከፍተኛ ደረጃ በአገሪቱ መስፋፋቱን፣ በተለይም በመሬት ንግድ ላይ እስከ አንገታቸው የተዘፈቁ ካድሬዎች መኖራቸውን የጠቆሙት ዶክተር መረራ፣ ኢሕአዴግ አሁን በያዘው አካሄድ የሰው ኃይሉን ለውጦ በግልጽነት አገር ይመራል የሚል ዕምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ኢሕአዴግ ለሕዝብ ያስተዋወቀው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የደርግ መንግሥት ሲያካሂደው ከነበረው ፕሮፓጋንዳ ተለይቶ እንደማይታይም አክለው ገልጸዋል፡፡

‹‹ኢሕአዴግ የሚያንቀሳቅሰው የሰው ኃይል በሙስና የተዘፈቀ ነው፡፡ ይህንን ኃይል ከሙስና ለማላቀቅ ኢሕአዴግ ሌላ አብዮት ሊያስፈልገው ይችላል፤ ዕቅዱን በተመለከተ ከባዶ ጫጫታ በላይ የሚታየኝ ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ኢሕአዴግ አሁን በያዛቸው ካድሬዎች በየዓመቱ 15 በመቶ ዕድገት ያመጣል ብሎ ማሰብ በሕልም ደረጃም ያስቸግራል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዶክተር መረራ እንደሚሉት፣ በአሁኑ ወቅት ያለው የዓለም ኢኮኖሚ ሁኔታ ኢትዮጵያ በየዓመቱ 15 በመቶ እንድታድግ የሚያስችላት አይደለም፡፡ ‹‹የዶላር ምንዛሪ ዋጋ ከፍ እንዲል መደረጉ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያመጣው አሉታዊ ተጽዕኖ አይኖርም፤›› የሚል ሐሳብ የሚሰነዝሩ ሰዎችን ሲሰሙ የሚገረሙ መሆናቸውን የጠቆሙት ዶክተር መረራ፣ የዶላር ምንዛሪ ዋጋ በጨመረ በጥቂት ቀናት ውስጥ በአገር ውስጥ ምርቶች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ በኢኮኖሚው ላይ ሊከሰት ለሚችለው ለውጥ ትክክለኛ ማሳያ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

መንግሥት ከሦስት ዓመት በፊት የደመወዝ ጭማሪ ሲያደርግ የእርሳቸው ደመወዝ በወቅቱ በነበረው ምንዛሪ 500 ዶላር ገደማ ደርሶ እንደነበር የገለጹት ዶክተር መረራ፣ በቅርቡ የዶላር ምንዛሪ እንዲጨምር ሲደረግ ግን ደመወዛቸው ተመልሶ ወደ 280 ዶላር ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት መንግሥት ወደ ፊት የ100 ፕርሰንት የደመወዝ ጭማሪ ቢያደርግ እንኳን የመንግሥት ተቀጣሪው ሠራተኛ የዛሬ ሶስት ዓመት ወደነበረበት ሁኔታ መመለሱ አይቀርም፡፡

የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት ሊቀመንበርና አቶ ገብሩ አስራት በበኩላቸው፣ ከልማት ዕቅድ ጋር በተያያዘ ኢሕአዴግ በተለይም ሕወሓት ሕዝቡን ሲያታልል መቆየቱን ለማየት ካስፈለገ የድርጅቱን የቅርብ ጊዜ ታሪክ መለስ ብሎ መቃኘት እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡

ሕወሓት በ1994 ዓ.ም በነደፈው መርሐ ግብር የትግራይ ሕዝብ ቢያንስ በሦስት ዓመት ውስጥ ቢበዛ ደግሞ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በምግብ ራሱን እንደሚችል፣ የእያንዳንዱ ቤተሰብ ዓመታዊ ገቢ 18 ሺሕ ብር እንደሚደርስ ዕቅዱን ለሕዝቡ አስተዋውቆ የተባለው ጊዜ ካለፈ በኋላም ሳይሳካ መቅረቱን ያስታወሱት አቶ ገብሩ፣ ኢሕአዴግ ቀደም ሲል የገባውን ቃል ረስቶ ‹‹ትራንስፎርሜሽን›› የሚል ሌላ ዕቅድ ይዞ መምጣቱ እንዳስገረማቸው ተናግረዋል፡፡

ትራንስፎርሜሽን ማለት ከፍተኛ እመርታ የሚታይበት እንቅስቃሴ መሆኑን የገለጹት አቶ ገብሩ፣ ‹‹ለእመርታ የሚሆን ምንም መሠረት ሳይጣል፣ ግብርናውም ሆነ ኢንዱስትሪው ምንም ዓይነት መዋቅራዊ ለውጥ ሳያመጣ፣ በበሬ እየታረሰ ከፍተኛ እመርታ ማስመዝገብ አይቻልም፡፡ ዕቅዱም ከፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ውጪ አይታይም፤›› ብለዋል፡፡ እንደ አቶ ገብሩ ገለጻ፣ መንግሥት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የምግብ ዋስትናን አረጋግጣለሁ ቢልም ዕቅዱን ለማስፈጸም የሚያስችል መሠረት አልጣለም፡፡

መንግሥት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ተግባራዊ ይሆናል ብሎ በያዘው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አገሪቱ በየዓመቱ 15 በመቶ እንደምታድግ፣ በምግብ እህል ራሷን ችላ ከስንዴ ልመና እንድትገላገልና ለዜጎቿና ለውጪ አገር ሰዎች ለኑሮ ምቹ ቦታ እንደምትሆን ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡ ዕቅዱን አስመልከተው በቅርቡ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ርብርብ ካላደረጉ በስተቀር ዕቅዱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይሆናል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር እንደማይቻል መናገራቸው ይታወሳል፡፡

lamrof
September 17th, 2010, 02:03 AM
2005 እ.ኤ.አ አቶ መለስ ዜናዊ በዜና ብዙኃን ቀርበው ኢትዮጵያ በ 5 ዓመታት ውስጥ ከአፍርካ ቀደምት የመረብ-ቅጥያ (broad band internet access) ካለባቸው አገሮች አንዷ ትሆናለች። ለዚህ እውንነት የጠለቀና የመጠቀ እቅድ ቀይሰናል ብለው ተና ገሩ። ከ 6 ዓመታት በኋላ እነሆ ኢትዮጵያ ከአፍሪቃም ሆነ ከአለም እጅግ አስከፊ እና ኋላ ቀር መረብ-ቅጥያ ያለባት ምናልባትም ከመጨረሻው ሁለተኛ አገር በመሆን ትገኛለች። በአሁኑ ግዜ የቴሌ ሥራ-አስኪያጅ የነበረው በእስር ላይ ሲገኝ እሱን ተክቶ ላለፉት 4 ዓመታት ሲያገለግል የነበረው ሥራውን ለቆ፣ የመስሪያ ቤቱ አስተዳደር በፈረንሳይ ኩባንያ ሹሞች በመተካት ላይ ይገኛል።

ይህ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ የመረብ መካነ-ድሮችን በማቀብ፣ የሬድዮ አየር ሞገዶችን በማቀብ የደርግ አይነት ሥራ በመስራቷ ያላት የዴሞክራሲያዊ እርከን ከምን ጊዜውም የበለጠ አሽቆልቁሎ ይገኛል። በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርሆ ሥር የግለኞች መብት እየተጣሰ ይገኛል። ጂ.ዲ.ፒ የሚለውን ትተን "ሂውማን ዲቬሎፕመንት" ወይም የዜጎችን ብቃት ወይም እድገት ደረጃ ስናይ ኢትዮጵያ በደርግ ዘመን ከነበረችበት ወርዳ ትገኛለች። ህዝቡ ከድጡ ወደ ማጡ ነው የሄደው። ይህንን እያየን እንዴት የለውጥ እቅድ እየተባለ ሲለፈፍ በሙሉ ልብ መተማመን እንችላለን?

ለውጥ የሚመጣው ዜጎችም አብረው ሲቀየሩ ነው። ህዝቡ የነጻነት እፎይታ እየተነፈሰ፣ የተሳትፎ ስሜቱ ልቆ፣ መንግሥት አገልጋይ እንጂ ተገልጋይ እንዳልሆነ በተግባር አይቶ አምኖ የአገሪቱን አቅጣጫ ወሳኝና ተቆጣጣሪ መሆኑን ሲተማመን ነው። ዛሬ የኢአዴግ አባል መሆን የመክበር ወይም የመደህየት ጥያቄ ነው። ይህንን ይዞ ነው ለውጥ የሚመጣው? አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከህብረተስብአዊነት ርእዮት ባለነሰ መንግሥትን አልቆ ህዝብን የሚያደቅ ሥርዓት ነው።

lamrof
September 17th, 2010, 02:04 AM
ደርግ የጦርነት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ፣ መውጫ ቀደዳ ሲያጣ ወደህዝቡ ዞሮ፣ አግዙኝ፣ ተባብረን ወንበዴን እናጥፋ፣ በርቱ-ተበራቱ፣ ለጦርነት ማገዶ የሚሆን የሰው ሃይል ስጡኝ እያለ ሲለፍፍ፣ የዜግነት ስሜቱን እንዳላዳሸቀ፣ የተሳትፎ ስሜቱን ደቁሶ እንዳላላመ፣ ሁሉን ረስቶ፣ አይኑን በጨው ታጥቦ ህዝቡን እርዱኝ እያለ ሲለማመን፣ አንድ ታላቅ ሰው ስብሰባ ላይ ወጥተው "መንግሥትና ህዝብ ሆድና ጀርባ ሆኗል" ብለው ያሉት ትዝ የለኛል።

ያለ ህዝብ መንፈሳዊ ቁርኝት መንግሥት ቢለፋ በአንድ እጅ ማጨብጨብ ነው የሚሆንበት። አብዮታዊ ዴሞክራሲ የኢህአዴግ ልእልና ማረጋገጫ ቁስ ነች ለማለት የሚያስደፍር ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። አገርን ማልማት ከዜጎች ልማት ጋር ተነጥሎ መሄድ የሚችል ነገር አይደለም.

ኢህአዴግ የብሔር ሀላዌነትና የግለሰብዕ ህላዌነትን በመሣ አያለሁ ይላል። ይሁንና ግን ግለሰብዓዊ ልእልናን ይሚጥሱ ተግባሮች በህግ ተደንግገው እናያለን። ግለሰቦችን የብሔር መለዮዋችሁን መታወቂያችሁ ላይ አስፍሩ ማለት እጅግ ዘግናኝ ነገር ነው። አሜሪካዊ ይሁዳውያንን የአይሁድ ሃይማኖት ተካታይ፣ ሙስሊሞችን እንዲሁ፣ ክርስቲያኖችንንም እንዲሁ እምነታችሁን መታወቂያችሁ ላይ አስፍሩ እንደማለት ይቆጠራል።

lamrof
September 17th, 2010, 02:05 AM
እጅግ ብዙ ኢትዮጵያውያን የኅብረ-ብሔር ትውልድ ዳራ አላቸው። ብሔራችሁን ምረጡ የሚለው ድንጋጌ ታዲያ የነሱን ፍላጎት መጣስ አይሆንም? እንዲህ ነው የግለሰብዕ ህላዌነት የሚከበረው? አንድ ኢትዮጵያዊ በፈለገው ክልል ውስጥ ያላንዳች ቅንቃኔ ሰርቶ የማደር መብት ሊኖረው ይገባል፣፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ይኽ አልሆነም ። ህዝቡ በኢትዮጵያዊነት ሳይሆን በብሔር መለዮ ሥር እንዲዳክር ተዳርጓል። በአሁኑ ይዘት ኢትዮጵያ የሃገራት ህብረት እንጂ አንድ ወጥ አገር አይደለችም። ቆይቶ የዜጎች ተገዢነት ለብሔር እንጂ ለሃገር አይሆንም። ይህንን መንፈስ ይዞ የመሻሻል እመርታ የለም።

lamrof
September 17th, 2010, 02:05 AM
የኢኣዴግ ችግር የመልካም ተልእኮ ችግር አይመስለኝም። የኢአዴግ ችግር የአመራሩን ልጓም የጨበጡት ሰዎች ሰፈውን አባልም ሆነ ህዝብ እንደሚነዳ ከብት ማየታቸው ነው። ሁሉም የኢህአዴግ ገንቢ ፓርቲዎች ህወኃትን ጨምሮ ከመሠረቱ የአመራር አካሉ በትምህርት ቀመስና ብሎም በምሁራን የተገነባ ሲሆን፣ ተከታይ ጀሌው መሃይምና በግርብርና ላይ የተሰማራ ነበር። እኛ እንምራ እናንተ ተዋጉ የሚለው አስተሳሰብ፣ እኛ በአእምሮ እንፈላሰፍ እናንተ በጉልበት ግልጋሎት ብቻ ትጉ ወደሚለው ሄዶ የመኳንንትና የጭሰኛ ሥርዓትን የያዘ ባህል ያሰረፀ ይመስላል።

ኢህአዴግ ደርግ ላይ የተቀዳጀውን ድል እንደገዛ ራሱ የውጊያ ልቀት ውጤጥ ብቻ ማየቱ ተገቢ አይደለም። ለደርግ መውደቅ ምክንያቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ደርግ ላይ የጣለው አሉታዊ ፍርጃም ጭምር ነው። ስልዚህ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ የላእላይነት ስሜት ከርሞ ለኢህአዴግም ለሃገሪቱም ውድቀት ይሆናልና ይታሰብበት። በአንፃሩም በተቃዋሚ ልሁቃን ላይ ያነጣጠረ የታህታይነት ስሜትና ፍራቻም በዚያው መጠን አደገኛ ነው።

ኢህአዴግ ነገሮችን አብጠርጥሮ የማየትና ከዚያም የመተለም ባህርይ ቢኖረውም አድራጎቱ ሁሉ ከራሱ እንጂ ከህዝብ ሉአላዊነት የመነጨ ስለአይደለ የማስፈጸም ችግር አለበት። ቅራቅንቦ ሰብስቦ፣ አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ እንደሚሄድ የጎዳና ተዳዳሪ ትልምን አጣርቶ የመፈጸም ታሪኩ ደካማ ነው። "ስንዴውን ጥላ ገለባውን" እንደሚባለው ከግብ ወቅት ሲደረስ ውጤቱ ውሽልሽል ነው። ለዚህ ሁሉ መፍትሄው ህዝብን ማክበርና ህዝብን ሉአላዊ ማድረግ ነው። አብዮታዊ ዴሞክራሲ ለዚህ መልስ ሊሆን አይችልም።

በአሁኑ ግዜ ኢትዮጵያን አጠባብቆ በአንድ ወጥ የያዘ የኢህአዴግ ህያውነት ነው ስልዚህ ኢህአዴግ እቅዱ እንዲሠምር እሻለሁ፣ ሆኖም ግን አንዳንድ የጠነዙ የአመለካከት ባህላቱን ካልተወ ስኬታማ ሊሆን አይችልም ይሚል ፍራቻ አለኝ። ለግለሰብዓትም ሆነ ለአሕዛብ ብልጽግና "ለጋስ ዴሞክራሲ" ለኢትዮጵያ ይገባል።